ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 3:19-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤

20. ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም።

21. በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”

22. ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱ፤ እዚያም ከእነርሱ ጋር ጥቂት ተቀመጠ፤ አጠመቀም።

23. በዚህ ጊዜ ዮሐንስም በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ብዙ ውሃ ስለ ነበረ፣ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር።

24. ይህም የሆነው ዮሐንስ ከመታሰሩ በፊት ነበር።

25. በአንዳንድ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአንድ አይሁዳዊ መካከል ስለ መንጻት ሥርዐት ክርክር ተነሣ፤

26. ወደ ዮሐንስም መጥተው፣ “ረቢ፤ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፣ ስለ እርሱም የመሰከርህለት ሰው፣ እነሆ ያጠምቃል፤ ሰውም ሁሉ ወደ እርሱ እየሄደ ነው” አሉት።

27. ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከላይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ሊቀበል አይችልም።

28. ‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ’ እንዳልሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ።

29. ሙሽራዪቱ የሙሽራው ነች፤ ድምፁን ለመስማት በአጠገቡ የሚቆመው ሚዜ ግን፣ የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፤ እርሱም አሁን ተፈጽሞአል።

30. እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል።

31. “ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነው የምድር ነው፤ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤

32. ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል፤ ነገር ግን ምስክርነቱን ማንም አይቀበልም፤

33. ምስክርነቱንም የተቀበለ ሰው፣ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደሆነ አረጋገጠ።

34. እግዚአብሔር መንፈሱን ሳይሰፍር ስለሚሰጥ፣ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል።

35. አብ ወልድን ይወዳል፤ ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል።

36. በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በላዩ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 3