ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 21:11-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ አምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም።

12. ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም።

13. ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ዓሣውንም ሰጣቸው።

14. እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነው።

15. በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወደኛለህን?” አለው።እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው።

16. ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወደኛለህን?” አለው።እርሱም፣ “አዎን፤ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው።

17. ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወደኛለህን?” አለው።ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ ‘ትወደኛለህን?’ ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው።ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ።

18. እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደማትፈልግበት ይወስድሃል።”

19. ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው።

20. ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ ራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 21