ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 19:30-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. ኢየሱስም ሆምጤውን ከተቀበለ በኋላ፣ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱን አዘንብሎ፣ መንፈሱን አሳልፎ ሰጠ።

31. ዕለቱ ለሰንበት መዘጋጃ ቀን ነበር። አይሁድ፣ የተሰቀሉት ሰዎች ሬሳ በሰንበት ቀን በመስቀል ላይ እንዳይውል ስለ ፈለጉና ያም የተለየ ሰንበት ስለ ነበር፣ የተሰቀሉት ሰዎች ጭናቸው ተሰብሮ በድናቸው እንዲወርድ ጲላጦስን ለመኑት።

32. ስለዚህም ወታደሮቹ መጥተው ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ የነበረውን የመጀመሪያውን ሰው ጭን ሰበሩ፤ ደግሞም የሌላውን ጭን ሰበሩ።

33. ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ሞቶ ስላገኙት ጭኖቹን አልሰበሩም፤

34. ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ የኢየሱስን ጐን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ፈሰሰ።

35. ይህን ያየው ሰው ምስክርነቱን ሰጥቶአል፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እውነትን እንደሚናገርም ያውቃል፤ እናንተም እንድታምኑ ይመሰክራል።

36. ይህም የሆነው፣ መጽሐፍ፣ “ከአጥንቱ አንድም አይሰበርም” ያለው እንዲፈጸም፣

37. ሌላውም መጽሐፍ፣ “የወጉትም ያዩታል” ስለሚል ነው።

38. ከዚህ በኋላ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን በድን ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነው፤ ዮሴፍም አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። እርሱም ጲላጦስን ካስፈቀደ በኋላ መጥቶ በድኑን ወሰደ።

39. ከዚህ ቀደም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ አንድ መቶ ሊትር ያህል የሚመዝን የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 19