ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 19:2-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ወታደሮችም የእሾህ አክሊል ጐንጒነው በራሱ ላይ አደረጉ፤ ሐምራዊ ልብስም አለበሱት፤

3. እየተመላለሱም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” አያሉ በጥፊ ይመቱት ነበር።

4. ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ውጭ ወጥቶ፣ “እንግዲህ ወደ እናንተ ያወጣሁት ለክስ የሚያደርስ ወንጀል እንዳላገኘሁበት እንድታውቁ ነው” አላቸው።

5. ኢየሱስ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ሐምራዊ ልብስም ለብሶ ወጣ፤ ጲላጦስም፣ “እነሆ፤ ሰውየው!” አላቸው።

6. የካህናት አለቆችና ሎሌዎቻቸውም ባዩት ጊዜ፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።ጲላጦስ ግን፣ “እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት፤ በእኔ በኩል ለክስ የሚያደርስ ወንጀል አላገኘሁበትም” አላቸው።

7. አይሁድም፣ “እኛ ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት አለበት” አሉ።

8. ጲላጦስ ይህን ሲሰማ የባሰውኑ ፈራ፤

9. ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” በማለት ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም።

10. ጲላጦስም፣ “አታናግረኝምን? ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው።

11. ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኀጢአት አለበት” አለው።

12. ከዚያ በኋላ ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ፈለገ፤ አይሁድ ግን፣ “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ የቄሣር ተቃዋሚ ነው” በማለት ጩኸታቸውን ቀጠሉ።

13. ጲላጦስም ይህን ሲሰማ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ ‘የድንጋይ ንጣፍ’ በተባለ፣ በአራማይክ ቋንቋ ‘ገበታ’ ብለው በሚጠሩት ስፍራ፣ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ።

14. ቀኑ የፋሲካ በዓል መዘጋጃ፣ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ያህል ነበር።ጲላጦስም አይሁድን፣ “እነሆ፤ ንጉሣችሁ” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 19