ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 17:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ፤ ጊዜው ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤

2. ከአንተ ለተቀበላቸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጥ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋልና።

3. እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።

4. የሰጠኸኝን ሥራ በመፈጸም በምድር አከበርሁህ።

5. እንግዲህ አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ።

6. “ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል።

7. የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደሆነ አሁን ዐውቀዋል፤

8. ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል፤ እኔም ከአንተ እንደ ወጣሁ በርግጥ ዐውቀዋል፤ አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል፤

9. እነርሱ የአንተ ስለሆኑ እጸልይላቸዋለሁ፤ ለሰጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም።

10. የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ።

11. ከእንግዲህ እኔ በዓለም አልቈይም፤ እነርሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፤ እኛ አንድ እንደሆንን፣ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 17