ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 16:6-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ይህን በመናገሬም ልባችሁ በሐዘን ተሞልቶአል፤

7. ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መሄዴ ይበጃችኋል። እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድሁ ግን እርሱን ወደ እናንተ እልካለሁ፤

8. በሚመጣበትም ጊዜ ዓለምን ስለ ኀጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ይወቅሳል።

9. ስለ ኀጢአት ሲባል፣ ሰዎች በእኔ ስለማያምኑ ነው፤

10. ስለ ጽድቅ፣ ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ስለማታዩኝ ነው፤

11. ስለ ፍርድም፣ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው።

12. “ብዙ የምነግራችሁ ነበረኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም።

13. የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤

14. የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል።

15. የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እንግዲህ፣ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ ያደርጋል’ ያልኋችሁ ለዚሁ ነው።”

16. “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ።”

17. ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ፣ “ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ እንዲሁም፣ ‘ወደ አብ ስለምሄድ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?” ተባባሉ፤

18. “‘ጥቂት ጊዜ’ ማለቱስ ምን ይሆን? የሚለውም ነገር አልገባንም” እያሉ ይጠያየቁ ነበር።

19. ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ባወቀ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ፣ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኋችሁ፣ ምን ማለቴ እንደሆነ እርስ በርሳችሁ ትጠያየቃላችሁ?

20. እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ሐሤት ያደርጋል፤ ይሁን እንጂ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።

21. ሴት ቀኗ ደርሶ ስትወልድ ትጨነቃለች፤ ከተገላገለች በኋላ ግን፣ ሰው ወደ ዓለም ስለ መጣ ጭንቋን ትረሳለች፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 16