ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 13:4-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ከእራት ተነሣ፤ መጐናጸፊያውን አስቀመጠ፤ ወገቡንም በፎጣ ታጠቀ።

5. ከዚያም በመታጠቢያው ውሃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር እያጠበ በታጠቀው ፎጣ ያብስ ጀመር።

6. ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እግሬን ታጥባለህ?” አለው።

7. ኢየሱስም መልሶ፣ “የማደርገውን አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው።

8. ጴጥሮስም፣ “የለም፤ እግሬን ከቶ አታጥብም” አለው።ኢየሱስም፣ “ካላጠብሁህማ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም” አለው።

9. ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም ራሴንም እጠበኝ” አለው።

10. ኢየሱስም፣ “ገላውን የታጠበ ሰው የሚያስፈልገው እግሩን ብቻ መታጠብ ነው፤ የቀረው አካሉ ግን ንጹሕ ነው። ሁላችሁም ባትሆኑ፣ እናንተ ንጹሓን ናችሁ” አለው።

11. “ሁላችሁም ንጹሓን አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው።

12. እግራቸውን አጥቦ ካበቃ በኋላም፣ ልብሱን ለብሶ ተመልሶ በቦታው ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?

13. እናንተ፣ ‘መምህርና፣ ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ ትክክል ነው፤ እንደምትሉኝ እንዲሁ ነኝና።

14. እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል።

15. እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ።

16. እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም።

17. እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 13