ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 13:19-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. “ሲፈጸም እኔ እንደሆንሁ ታምኑ ዘንድ፣ ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን ነገርኋችሁ።

20. እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የላክሁትን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔን የተቀበለም የላከኝን ይቀበላል።”

21. ይህን ካለ በኋላም ኢየሱስ በመንፈሱ ታውኮ፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” ሲል በግልጽ ተናገረ።

22. ደቀ መዛሙርቱም ማንን ማለቱ እንደሆነ ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው ተያዩ።

23. ከእነርሱ አንዱ፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ ተቀምጦ ነበር።

24. ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ደቀ መዝሙር በምልክት ጠቅሶ “ማንን ማለቱ እንደሆነ ጠይቀው” አለው።

25. እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ደገፍ ብሎ፣ “ጌታ ሆይ፤ ማን ይሆን?” ብሎ ጠየቀው።

26. ኢየሱስም፣ “ይህን ቊራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አለው፤ ከዚያም ቊራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው።

27. ይሁዳም ቊራሹን እንጀራ እንደ ተቀበለ ወዲያው ሰይጣን ገባበት።ኢየሱስም፣ “የምታደርገውን ቶሎ አድርግ” አለው፤

28. ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለምን እንዲህ እንዳለው ማንም አላወቀም ነበረ።

29. ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበር፣ አንዳንዶቹ ለበዓሉ የሚያስፈልግ ነገር እንዲገዛ ወይም ለድኾች እንዲሰጥ ኢየሱስ የተናገረው መሰላቸው።

30. ይሁዳም ያን ቊራሽ እንጀራ እንደ ተቀበለ ወጥቶ ሄደ፤ ሌሊትም ነበረ።

31. ይሁዳ ከወጣ በኋላ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ በእርሱም እግዚአብሔር ከበረ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 13