ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 11:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ኢየሱስም ማርታን፣ እኅቷንና አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር።

6. ሆኖም አልዓዛር መታመሙን በሰማ ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ቈየ።

7. ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደ ይሁዳ እንመለስ” አላቸው።

8. እነርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት አይሁድ በድንጋይ ሊወግሩህ እየፈለጉህ ነበር፤ እንደ ገና ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት።

9. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ብርሃን አይደለምን? ከዚህ ዓለም ብርሃን የተነሣ ስለሚያይ በቀን የሚመላለስ አይሰናከልም፤

10. የሚሰናከለው ግን በሌሊት የሚመላለስ ነው፤ ብርሃን የለውምና።”

11. ይህን ከነገራቸው በኋላ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው።

12. ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ ተኝቶ ከሆነስ ይድናል” አሉት።

13. ኢየሱስ ይህን የነገራቸው ስለ ሞቱ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን እንቅልፍ ስለ መተኛቱ የተናገረ መሰላቸው።

14. ስለዚህም በግልጽ እንዲህ አላቸው፤ “አልዓዛር ሞቶአል፤

15. ታምኑ ዘንድ፣ በዚያ ባለ መኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ።”

16. ከዚያም ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ለተቀሩት ደቀ መዛሙርት፣ “እኛም ሄደን ከእርሱ ጋር እንሙት” አላቸው።

17. ኢየሱስ ሲደርስ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 11