ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 10:24-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. አይሁድም ከበውት፣ “እስከ መቼ ልባችንን አንጠልጥለህ ታቈየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጽ ንገረን” አሉት።

25. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሳላቸው፤ “እኔ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ታምራትም ስለ እኔ ይናገራሉ፤

26. እናንተ ግን በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም፤

27. በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤

28. እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም።

29. እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም።

30. እኔና አብ አንድ ነን።”

31. አይሁድ ሊወግሩት እንደ ገና ድንጋይ አነሡ፤

32. ኢየሱስ ግን፣ “ከአብ የሆኑ ብዙ ታላላቅ ታምራትን አሳየኋችሁ፤ ታዲያ ከእነዚህ ስለ የትኛው ትወግሩኛላችሁ?” አላቸው።

33. አይሁድም፣ “የምንወግርህ፣ ተራ ሰው ሆነህ ሳለህ፣ ራስህን አምላክ በማድረግ፣ የስድብ ቃል ስለተናገርህ ነው እንጂ ከእነዚህ ስለ የትኛውም አይደለም” ብለው መለሱለት።

34. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በሕጋችሁ፣ ‘እናንት አማልክት ናችሁ አልሁ’ ተብሎ አልተጻፈምን?

35. የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ‘አማልክት’ ካላቸውና መጻሕፍም ሊሻር የማይቻል ከሆነ፣

36. ታዲያ፣ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስላልሁ፣ አብ ለራሱ ለይቶ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን፣ ተሳድበሃል ብላችሁ ለምን ትወነጅሉኛላችሁ?

37. አባቴ የሚያደርገውን ባላደርግ አትመኑኝ፤

38. የማደርገው ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ፣ አብ በእኔ እንዳለ እኔም በአብ እንዳለሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ታምራቱን እመኑ።”

39. እንደ ገናም ሊይዙት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አመለጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 10