ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 10:19-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ከዚህም ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ተፈጠረ።

20. ብዙዎቹም፣ “ጋኔን ያደረበት እብድ ነው፤ ለምን ትሰሙ ታለችሁ?” አሉ።

21. ሌሎች ግን፣ “ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው ንግግር አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ።

22. በኢየሩሳሌምም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ጊዜውም ክረምት ነበረ፤

23. ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ግቢ፣ በሰሎሞን መመላለሻ ያልፍ ነበር፤

24. አይሁድም ከበውት፣ “እስከ መቼ ልባችንን አንጠልጥለህ ታቈየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጽ ንገረን” አሉት።

25. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሳላቸው፤ “እኔ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ታምራትም ስለ እኔ ይናገራሉ፤

26. እናንተ ግን በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም፤

27. በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤

28. እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም።

29. እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም።

30. እኔና አብ አንድ ነን።”

31. አይሁድ ሊወግሩት እንደ ገና ድንጋይ አነሡ፤

32. ኢየሱስ ግን፣ “ከአብ የሆኑ ብዙ ታላላቅ ታምራትን አሳየኋችሁ፤ ታዲያ ከእነዚህ ስለ የትኛው ትወግሩኛላችሁ?” አላቸው።

33. አይሁድም፣ “የምንወግርህ፣ ተራ ሰው ሆነህ ሳለህ፣ ራስህን አምላክ በማድረግ፣ የስድብ ቃል ስለተናገርህ ነው እንጂ ከእነዚህ ስለ የትኛውም አይደለም” ብለው መለሱለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 10