ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 1:39-51 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

39. እርሱም፣ “ኑና እዩ” አላቸው።ስለዚህ ሄደው የት እንደሚኖር አዩ፤ በዚያም ዕለት አብረውት ዋሉ፤ ከቀኑም ዐሥር ሰዓት ያህል ነበር።

40. ዮሐንስ የተናገረውን ሰምተው፣ ኢየሱስን ከተከሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበር።

41. እንድርያስ በመጀመሪያ ያደረገው ወንድሙን ስምዖንን ፈልጎ፣ “መሲሑን አገኘነው” ብሎ መንገር ነው፤ ‘መሲሕ’ ማለት ክርስቶስ ማለት ነው።

42. ወደ ኢየሱስም አመጣው።ኢየሱስም ተመለከተውና፣ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ ኬፋ ተብለህ ትጠራለህ” አለው፤ ‘ኬፋ’ ማለት ጴጥሮስ ማለት ነው።

43. በማግሥቱ፣ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አግኝቶ፣ “ተከተለኝ” አለው።

44. ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ።

45. ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፣ “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል” አለው።

46. ናትናኤልም፣ “ከናዝሬት በጎ ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለ።ፊልጶስም፣ “መጥተህ እይ” አለው።

47. ኢየሱስም፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ፣ “እነሆ፤ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” አለ።

48. ናትናኤልም “እንዴት አወቅኸኝ?” ሲል ጠየቀው።ኢየሱስም፣ “ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ፣ ገና ፊሊጶስ ሳይጠራህ አየሁህ” ሲል መለሰለት።

49. ናትናኤልም መልሶ፣ “ረቢ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ።

50. ኢየሱስም፣ “ያመንኸው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልሁህ ነውን? ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ” አለው፤

51. ጨምሮም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ፣ የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 1