ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 1:29-42 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. ዮሐንስ በማግሥቱ፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤

30. ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልሁት እርሱ ነው፤

31. እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው።”

32. ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤

33. በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤

34. አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እመሰክራለሁ።”

35. በማግሥቱ፣ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤

36. ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ! የእግዚአብሔር በግ” አለ።

37. ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።

38. ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉት አየና፣ “ምን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ረቢ፣ የት ትኖራለህ?” አሉት፤ ‘ረቢ’ ማለት መምህር ማለት ነው።

39. እርሱም፣ “ኑና እዩ” አላቸው።ስለዚህ ሄደው የት እንደሚኖር አዩ፤ በዚያም ዕለት አብረውት ዋሉ፤ ከቀኑም ዐሥር ሰዓት ያህል ነበር።

40. ዮሐንስ የተናገረውን ሰምተው፣ ኢየሱስን ከተከሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበር።

41. እንድርያስ በመጀመሪያ ያደረገው ወንድሙን ስምዖንን ፈልጎ፣ “መሲሑን አገኘነው” ብሎ መንገር ነው፤ ‘መሲሕ’ ማለት ክርስቶስ ማለት ነው።

42. ወደ ኢየሱስም አመጣው።ኢየሱስም ተመለከተውና፣ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ ኬፋ ተብለህ ትጠራለህ” አለው፤ ‘ኬፋ’ ማለት ጴጥሮስ ማለት ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 1