ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ይሁዳ 1:5-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ምንም እንኳ አስቀድማችሁ ይህን ሁሉ የምታውቁ ቢሆንም፣ ጌታ ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዴት እንዳወጣ፣ በኋላ ግን ያላመኑትን እንዳጠፋ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።

6. የሥልጣን ስፍራቸውን ያልጠበቁትን ነገር ግን መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት በዘላለም እስራት እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ በጨለማ ጠብቆአቸዋል።

7. እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ፣ በዙሪያቸውም ያሉ ከተሞች ለሴሰኛነትና ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ ለሆነ ሩካቤ ሥጋ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ እነርሱም በዘላለም እሳት በመቀጣት ለሚሠቃዩት ምሳሌ ሆነዋል።

8. በዚህ ሁኔታ እነዚህ ሕልም አላሚዎች የገዛ ሥጋቸውን ያረክሳሉ፤ ሥልጣንን ይቃወማሉ፤ በሰማይ ክብር ያላቸውንም ፍጥረታት ይሳደባሉ።

9. የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል እንኳ ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ፣ “ጌታ ይገሥጽህ” አለው እንጂ የስድብ ቃል በመናገር ሊከሰው አልደፈረም።

10. እነዚህ ሰዎች ግን የማያውቁትን ነገር ሁሉ ይሳደባሉ፤ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት በደመ ነፍስ በሚያወቁት ነገር ይጠፋሉ።

11. ወዮላቸ በቃየን መንገድ ሄደዋል፤ ለገንዘብ ሲስገበገቡ በበለዓም ስሕተት ውስጥ ወድቀዋል፤ በቆሬም ዐመፅ ጠፍተዋል።

12. እነዚህ ሰዎች በፍቅር ግብዣችሁ ላይ ያለ አንዳች ኀፍረት ከእናንተ ጋር ቀርበው የሚበሉ ነውረኞች ናቸው፤ ደግሞም ራሳቸውን ብቻ የሚመግቡ እረኞች ናቸው፤ እነርሱም በነፋስ የሚነዱ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ናቸው፤ በመከር ወራት ፍሬ የማይገኝባቸው ከሥራቸው ተነቅለው ሁለት ጊዜ የሞቱ ዛፎች ናቸው።

13. የነውራቸውን አረፋ የሚደፍቁ የተቈጡ የባሕር ማዕበል፣ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የሚጠብቃቸው ተንከራታች ከዋክብት ናቸው።

14. ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነው ሄኖክ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ሲል ተንብዮአል፤ “እነሆ፤ ጌታ ከእልፍ አእላፋት ቅዱሳኑ ጋር ይመጣል፤

15. ይህም፣ በሰው ሁሉ ላይ ለመፍረድ እንዲሁም ዐመፀኞችን ሁሉ በክፋት መንገድ በሠሩት የዐመፅ ሥራና በክፋት በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩት የስድብ ቃል ሁሉ አጥፊነታቸውን ይፋ ለማድረግ ነው”።

16. እነዚህ ሰዎች የሚያጒረመርሙና ሌሎችን ሰዎች የሚከሱ ናቸው፤ ርኩስ ምኞታቸውን ይከተላሉ፤ በራሳቸው ይታበያሉ፤ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሌሎችን ይክባሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ይሁዳ 1