ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ይሁዳ 1:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እነዚህ ሰዎች የሚያጒረመርሙና ሌሎችን ሰዎች የሚከሱ ናቸው፤ ርኩስ ምኞታቸውን ይከተላሉ፤ በራሳቸው ይታበያሉ፤ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሌሎችን ይክባሉ።

17. ነገር ግን ወዳጆች ሆይ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የተናገሩትን አስታውሱ።

18. እነርሱም፣ “በመጨረሻው ዘመን ርኩስ ምኞታቸውን የሚከተሉ ዘባቾች ይመጣሉ” ብለዋችኋል።

19. እነዚህ ሰዎች በመካከላችሁ መለያየትን የሚፈጥሩ፣ በደመ ነፍስ የሚነዱ መንፈስ የሌላቸው ናቸው።

20. እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፤ እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸልዩ።

21. ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሳችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።

22. ተጠራጣሪ ለሆኑት ራሩላቸው፤

23. አንዳንዶችን ከእሳት ነጥቃችሁ አድኗቸው፤ ለሌሎች ደግሞ በርኩስ ሥጋ የተበከለውን ልብሳቸውን እንኳ እየጠላችሁ በፍርሀት ምሕረት አሳዩአቸው።

24. እንዳትወድቁ ሊጠብቃችሁና ያለ ነቀፋና በደስታ በክብሩ ፊት ሊያቀርባችሁ ለሚችለው፣

25. እርሱ ብቻ አዳኛችን ለሆነው አምላክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከዘመናት ሁሉ በፊት፣ አሁንና እስከ ዘላለምም ድረስ ክብር፣ ግርማ፣ ኀይልና ሥልጣን ይሁን፤ አሜን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ይሁዳ 1