ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ይሁዳ 1:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፤ለተጠሩት፣ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስ ለተጠበቁት፤

2. ምሕረት፣ ሰላምና ፍቅር ይብዛላችሁ።

3. ወዳጆች ሆይ፤ አብረን ስለምንካፈለው ድነት ልጽፍላችሁ እጅግ ጓጒቼ ነበር፤ ነገር ግን ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ ስለ ተሰጠው እምነት እንድትጋደሉ ለመምከር እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።

4. ከረጅም ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ገብተዋልና፤ እነርሱ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ የአምላካችንን ጸጋ በርኵሰት የሚለውጡና እርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።

5. ምንም እንኳ አስቀድማችሁ ይህን ሁሉ የምታውቁ ቢሆንም፣ ጌታ ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዴት እንዳወጣ፣ በኋላ ግን ያላመኑትን እንዳጠፋ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።

6. የሥልጣን ስፍራቸውን ያልጠበቁትን ነገር ግን መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት በዘላለም እስራት እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ በጨለማ ጠብቆአቸዋል።

7. እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ፣ በዙሪያቸውም ያሉ ከተሞች ለሴሰኛነትና ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ ለሆነ ሩካቤ ሥጋ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ እነርሱም በዘላለም እሳት በመቀጣት ለሚሠቃዩት ምሳሌ ሆነዋል።

8. በዚህ ሁኔታ እነዚህ ሕልም አላሚዎች የገዛ ሥጋቸውን ያረክሳሉ፤ ሥልጣንን ይቃወማሉ፤ በሰማይ ክብር ያላቸውንም ፍጥረታት ይሳደባሉ።

9. የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል እንኳ ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ፣ “ጌታ ይገሥጽህ” አለው እንጂ የስድብ ቃል በመናገር ሊከሰው አልደፈረም።

10. እነዚህ ሰዎች ግን የማያውቁትን ነገር ሁሉ ይሳደባሉ፤ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት በደመ ነፍስ በሚያወቁት ነገር ይጠፋሉ።

11. ወዮላቸ በቃየን መንገድ ሄደዋል፤ ለገንዘብ ሲስገበገቡ በበለዓም ስሕተት ውስጥ ወድቀዋል፤ በቆሬም ዐመፅ ጠፍተዋል።

12. እነዚህ ሰዎች በፍቅር ግብዣችሁ ላይ ያለ አንዳች ኀፍረት ከእናንተ ጋር ቀርበው የሚበሉ ነውረኞች ናቸው፤ ደግሞም ራሳቸውን ብቻ የሚመግቡ እረኞች ናቸው፤ እነርሱም በነፋስ የሚነዱ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ናቸው፤ በመከር ወራት ፍሬ የማይገኝባቸው ከሥራቸው ተነቅለው ሁለት ጊዜ የሞቱ ዛፎች ናቸው።

13. የነውራቸውን አረፋ የሚደፍቁ የተቈጡ የባሕር ማዕበል፣ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የሚጠብቃቸው ተንከራታች ከዋክብት ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ይሁዳ 1