ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ያዕቆብ 4:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጉት ምኞታችሁ አይደለምን?

2. ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም። ትገድላላችሁ፤ በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም። ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ፤ አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም።

3. ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና።

4. አመንዝሮች ሆይ፤ ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደሆነ አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።

5. ወይስ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል በማለት መጽሐፍ የተናገረው በከንቱ ይመስላችኋልን?

6. ነገር ግን ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል፤ መጽሐፍም፣“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል”ያለው ስለዚህ ነው።

7. እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል።

8. ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ።

9. ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፣ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ።

10. በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።

11. ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ያዕቆብ 4