ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ያዕቆብ 2:14-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረውምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን?

15. አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው፣

16. ከእናንተ መካከል አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል?

17. እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው።

18. ነገር ግን አንድ ሰው “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ሥራ አለኝ” ይላል።እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ።

19. አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ።

20. አንተ ከንቱ ሰው! እምነት ያለ ሥራ ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ማስረጃ ትፈልጋለህን?

21. አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን?

22. በዚህም እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበር ታያለህ፤ እምነትም በሥራ ፍጹም ሆነ።

23. “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ያዕቆብ 2