ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 9:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. የመጀመሪያዪቱ ድንኳን ቆማ እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።

9. ይህም ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ ሲሆን፣ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም ሊያደርጉ አልቻሉም።

10. እነዚህ ሁሉ አዲሱ ሥርዐት እስኪመጣ ድረስ የሚደረጉ የምግብና የመጠጥ እንዲሁም የተለያዩ የመንጻት ሥርዐቶች ብቻ ናቸው።

11. ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳ ልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ።

12. የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ።

13. የውጭ አካላቸው ይነጻ ዘንድ በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጨው የፍየሎችና የኮርማዎች ደም እንዲሁም የፍየሎችና የጊደር ዐመድ የሚቀድሳቸው ከሆነ፣

14. በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!

15. ስለዚህም የተጠሩት፣ ተስፋ የተሰጠውን የዘላለም ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፤ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ ከሠሩት ኀጢአት ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቶአልና።

16. ኑዛዜ በሚኖርበት ጊዜ የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ግድ ነው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕብራውያን 9