ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 9:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የመጀመሪያው ኪዳን የአምልኮ ሥርዐትና ምድራዊ መቅደስ ነበረው።

2. ድንኳን ተተክሎ ነበር፤ በመጀመሪያው ክፍል መቅረዙ፣ ጠረጴዛውና የመሥዋዕቱ ኅብስት ነበረበት፤ ይህም ስፍራ ቅድስት ይባላል።

3. ከሁለተኛው መጋረጃ በስተ ኋላ ቅድስተ ቅዱሳን የተባለ ክፍል ነበር፤

4. በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንትና በወርቅ የተለበጠው የኪዳኑ ታቦት ነበሩ፤ ይህም ታቦት መና ያለበትን የወርቅ መሶብ፣ የለመለመችውን የአሮንን በትርና ኪዳኑ የተጻፈበትን ጽላት ይዞአል።

5. በታቦቱም ላይ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ አሁን ግን ስለ እነዚህ ነገሮች በዝርዝር መናገር አንችልም።

6. ሁሉም በዚህ መልክ ከተዘጋጀ በኋላ፣ ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ዘወትር ወደ ድንኳኒቱ መጀመሪያ ክፍል ይገባሉ።

7. ነገር ግን ወደ ውስጠኛው ክፍል የሚገባው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ስለ ራሱ ኀጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኀጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ ከቶ አይገባም ነበር።

8. የመጀመሪያዪቱ ድንኳን ቆማ እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።

9. ይህም ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ ሲሆን፣ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም ሊያደርጉ አልቻሉም።

10. እነዚህ ሁሉ አዲሱ ሥርዐት እስኪመጣ ድረስ የሚደረጉ የምግብና የመጠጥ እንዲሁም የተለያዩ የመንጻት ሥርዐቶች ብቻ ናቸው።

11. ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳ ልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕብራውያን 9