ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 7:2-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. አብርሃምም ከሁሉ ነገር ዓሥራት አውጥቶ ሰጠው። በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ኋላም ደግሞ “የሳሌም ንጉሥ” ማለትም “የሰላም ንጉሥ ማለት” ነው።

3. አባትና እናት ወይም የትውልድ ሐረግ የለውም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ልጅ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።

4. እስቲ እርሱ የቱን ያህል ታላቅ እንደሆነ ዐስቡ፤ ርእሰ አበው የሆነው አብርሃም እንኳ ካገኘው ምርኮ ዓሥራት አውጥቶ ሰጠው።

5. ክህነት የተሰጣቸው የሌዊ ልጆች ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም፣ ከሕዝቡ ማለት ከገዛ ወንድሞቻቸው ዓሥራት እንዲቀበሉ ሕጉ ያዛል።

6. ይህ ግን ትውልዱ ከሌዊ ወገን አይደለም፤ ይሁን እንጂ ከአብርሃም ዓሥራት ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተቀበለውንም ባረከው።

7. ትንሹ በትልቁ እንደሚባረክ ጥርጥር የለውም።

8. በአንድ በኩል ዓሥራት የሚቀበሉት ሟች ሰዎች ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት ይቀበላል።

9. እንዲያውም ዓሥራት የሚቀበለው ሌዊ፣ ራሱ በአብርሃም በኩል ዓሥራት ከፍሎአል ማለት ይቻላል፤

10. ምክንያቱም መልከጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ፣ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ነበር።

11. ፍጹምነት የተገኘውና ሕጉ ለሕዝቡ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣቱ ለምን አስፈለገ?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕብራውያን 7