ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 5:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. አሮን እንደ ተጠራ በእግዚአብሔር መጠራት አለበት እንጂ፣ ይህን ክብር ለራሱ የሚወስድ ማንም የለም።

5. እንዲሁም ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የመሆንን ክብር ለራሱ አልወሰደም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር፣“አንተ ልጄ ነህ፤እኔ ዛሬ አባት ሆንሁህ” አለው።

6. እንዲሁም በሌላ ስፍራ፣“እንደ መልከጼዴቅ ሹመት፣አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ይላል።

7. ኢየሱስ በዚህ ምድር በኖረበት ዘመን ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋር አቀረበ፤ ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት።

8. የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እንኳ፣ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤

9. በዚህም ፍጹም ሆኖ ከተገኘ በኋላ፣ እርሱን ለሚታዘዙ ሁሉ የዘላለም ድነት ምክንያት ሆነላቸው፤

10. እንደ መልከጸዴቅ ሹመትም ሊቀ ካህናት ተብሎ በእግዚአብሔር ተሾመ።

11. ስለዚህ ጉዳይ የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ነገር ግን ለመማር ዳተኛ ስለ ሆናችሁ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው።

12. በዚህ ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፣ ገና የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያ ትምህርት የሚያስተምራችሁ ሰው ያስፈልጋችኋል፤ የሚያስፈልጋችሁም ጠንካራ ምግብ ሳይሆን ወተት ነው።

13. ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ፣ ከጽድቅ ትምህርት ጋር ገና አልተዋወቀም።

14. ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ላስለመዱ፣ ለበሰሉ ሰዎች ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕብራውያን 5