ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 4:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እኛ ያመንነው ግን ወደዚያ ዕረፍት እንገባለን፤ እግዚአብሔርም፣“ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤‘ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም’ ” ብሎአል።ይሁን እንጂ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የእርሱ ሥራ ተከናውኖአል።

4. ስለ ሰባተኛውም ቀን በአንድ ስፍራ፣ “በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሎአልና።

5. ቀደም ባለው ክፍል ደግሞ፣“ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም” ይላል።

6. ወደ ዕረፍቱ ገና የሚገቡ አንዳንዶች አሉ፤ ቀድሞ የምሥራቹ ቃል የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ወደ ዕረፍት አልገቡም።

7. ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “ዛሬ” ብሎ እንደ ገና አንድን ቀን ወሰነ፤ ይህም ከብዙ ዘመን በኋላ በዳዊት በኩል፣“ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ልባችሁን አታደንድኑ”ተብሎ ቀደም ሲል እንደ ተነገረው ነው።

8. ኢያሱ ዕረፍትን ሰጥቶአቸው ቢሆን ኖሮ፣ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ስለ ሌላ ቀን ባል ተናገረ ነበር።

9. ስለዚህ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ገና ቀርቶለታል፤

10. ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት የሚገባ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱም ደግሞ ከሥራው ያርፋል።

11. እንግዲህ ማንም የእነዚያን አለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።

12. የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕብራውያን 4