ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 13:17-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጒዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው። አለበለዚያ አይበጃችሁም።

18. ለእኛ ደግሞ ጸልዩልን። በሁሉም መንገድ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚናፍቅ ንጹሕ ኅሊና እንዳለን ርግጠኞች ነን።

19. በተለይም ወደ እናንተ በፍጥነት ተመልሼ እንድመጣ ትጸልዩል ዘንድ ዐደራ እላችኋለሁ።

20. በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ፣

21. ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ ደስ የሚያሰኘውንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ያድርግ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።

22. ወንድሞች ሆይ፤ የጻፍሁላችሁ መልእክት አጭር እንደ መሆኑ፣ የምክር ቃሌን በትዕግሥት እንድትቀበሉ ዐደራ እላችኋለሁ።

23. ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደተፈታ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ፤ ቶሎ ከመጣ፣ ከእርሱ ጋር ላያችሁ እመጣለሁ።

24. ለመሪዎቻችሁ ሁሉና ለቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከኢጣሊያ የሆኑትም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

25. ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕብራውያን 13