ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 13:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች ተዋደዱ።

2. እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ፣ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋልና።

3. በእስር ላይ ያሉትን ከእነርሱ ጋር እንደታሰራችሁ ሆናችሁ ዐስቡአቸው፤ እንዲሁም በሰው እጅ የሚንገላቱትን ራሳችሁ መከራ እንደምትቀበሉ አድርጋችሁ ዐስቡአቸው።

4. ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአመንዝሮችና በሴሰኞች ሁሉ ላይ ይፈርዳል።

5. ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣“ከቶ አልተውህም፤በፍጹም አልጥልህም” ብሎአል።

6. ስለዚህ በሙሉ ልብ፣“ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።

7. የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን ዐስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሉአቸው።

8. ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው።

9. በልዩ ልዩ ዐይነት እንግዳ ትምህርቶች አትወሰዱ፤ ልባችን የሚጸናው በጸጋ እንጂ የምግብ ሥርዐት በመጠበቅ አይደለም፤ ይህንን ሥርዐት የሚጠብቁት እንኳ በዚህ አልተጠቀሙም።

10. በድንኳኒቱም የሚያገለግሉ ከዚያ ሊበሉ መብት ያላገኙበት መሠዊያ አለን።

11. ሊቀ ካህናቱ ስለ ኀጢአት ስርየት የሚሆነውን የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፤ የእንስሳቱ ሥጋ ግን ከሰፈር ውጭ ይቃጠላል።

12. እንዲሁም ኢየሱስ በራሱ ደም አማካይነት ሕዝቡን ሊቀድስ ከከተማው በር ውጭ መከራን ተቀበለ።

13. ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከመውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ።

14. ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕብራውያን 13