ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 12:14-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም፤

15. ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ።

16. ለአንድ ጊዜ መብል ሲል ብኵርናውን እንደ ሸጠው እንደ ዔሳው ማንም ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።

17. በኋላም ይህንኑ በረከት ሊወርስ በፈለገ ጊዜ፣ እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ በረከቱን በእንባ ተግቶ ቢፈልግም መልሶ ሊያገኘው አልቻለም።

18. ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደሚቃጠለው ተራራ፣ ወደ ጨለማው፣ ወደ ጭጋጉና ወደ ዐውሎ ነፋሱ አልደረሳችሁም፤

19. ወደ መለከት ድምፅ፣ ወይም ቃልን ወደ ሚያሰማ ድምፅ አልመጣችሁም፤ የሰሙትም ሌላ ቃል ተጨምሮ እንዳይናገራቸው ለመኑ።

20. ምክንያቱም “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ፣ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት” የሚለውን ትእዛዝ መሸከም አልቻሉም።

21. በዚያ ይታይ የነበረውም ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነበርና፣ ሙሴ “በፍርሀት ተንቀጠቀጥሁ” አለ።

22. እናንተ ግን ወደ ጽዮን ተራራ፣ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም፣ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ መጥታችኋል፤ በደስታ ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፣

23. ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈው ወደ በኵራት ማኅበር ቀርባችኋል፤ የሁሉ ዳኛ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር፣ ፍጹምነትን ወዳገኙት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፣

24. የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ፣ እንዲሁም ከአቤል ደም የተሻለ ቃል ወደሚናገረው ወደ ተረጨው ደም ደርሳችኋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕብራውያን 12