ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤፌሶን 6:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ልጆች ሆይ፤ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና።

2. “አባትህንና እናትህን አክብር” በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣

3. “መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” የሚል ነው።

4. አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።

5. ባሪያዎች ሆይ፤ ለክርስቶስ እንደምት ታዘዙ፣ በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑት በአክብሮትና በፍርሀት፣ በልብ ቅንነትም ታዘዙ፤

6. ለታይታና ከእነርሱ ሙገሳን ለማግኘት ሳይሆን እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ በመፈጸም ታዘዟቸው።

7. ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ ሆናችሁ በሙሉ ልብ አገልግሉ፤

8. ምክንያቱም፣ ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ።

9. እናንተም ጌቶች ሆይ፤ ለባሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የእነርሱም፣ የእናንተም ጌታ የሆነው በሰማይ እንዳለ፣ የሰውንም ፊት አይቶ እንደማያደላ ታውቃላችሁና አታስፈራሯቸው።

10. በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤፌሶን 6