ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤፌሶን 5:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤

2. ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ።

3. ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኵሰት ወይም የስስት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና።

4. የሚያሳፍርና ተራ የሆነ ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛም ለእናንተ ስለማይገባ በመካከላችሁ አይኑር፤ ይልቁንስ የምታመሰ ግኑ ሁኑ።

5. ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ ይኸውም ጣዖት አምላኪ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም።

6. ማንም በከንቱ ንግግር አያታላችሁ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቊጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚመጣው በእንደዚህ ዐይነት ነገር ነው።

7. ስለዚህ እንዲህ ካሉ ጋር አትተባበሩ።

8. ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤

9. የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና።

10. እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ።

11. ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት አይኑራችሁ፤ ይልቁን ግለጡት፤

12. በድብቅ የሚሠሩትን ነገር መናገር ራሱ አሳፋሪ ነውና።

13. ብርሃን የበራበት ነገር ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤

14. ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣“አንተ የተኛህ ንቃ፤ከሙታን ተነሣ፤ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሎአል።

15. እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ።

16. ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ።

17. ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ።

18. በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤፌሶን 5