ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤፌሶን 3:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. አሳቡም በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት አለቆችና ባለ ሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው፤

11. ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን በፈጸመው ዘላለማዊ ዕቅዱ መሠረት ነው።

12. በእርሱና በእርሱ ላይ ባለን እምነት አማካይነት፣ በነጻነትና በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን።

13. ስለዚህ ክብራችሁ በሆነው ስለ እናንተ በደረሰብኝ መከራ ተስፋ እንዳትቈርጡ ዐደራ እላችኋለሁ።

14. በዚህም ምክንያት በአብ ፊት እንበረከ ካለሁ፤

15. ከእርሱም በሰማይና በምድር ያለ ቤተ ሰብ ሁሉ ስያሜ ያገኛል።

16. በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤

17. ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣

18. የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው።

19. እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው።

20. እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣

21. በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን፤ አሜን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤፌሶን 3