ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤፌሶን 2:9-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም፤

10. ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀልንን መልካም ሥራ እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።

11. ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የሆናችሁ፣ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፣ ራሳቸውን “ተገርዘናል” በሚሉት፣ “ያልተገረዙ” የተባላችሁ ያን አስታውሱ፤

12. በዚያን ዘመን ከክርስቶስ ተለይታችሁ፣ ከእስራኤል ወገንነት ርቃችሁ፣ ለኪዳኑም ተስፋ ባዕዳን ሆናችሁ፣ በዓለም ላይ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር እንደ ነበራችሁ አስታውሱ።

13. አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል።

14. ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና፤

15. ሕግንም፣ ከትእዛዛቱና ከሥርዐቱ ጋር በሥጋው ሻረ። ዐላማውም ከሁለቱ አንድን አዲስ ሰው በራሱ ፈጥሮ ሰላምን ለማድረግ ነው።

16. ጥልን በገደለበት በመስቀሉም ሁለቱን በዚህ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ።

17. መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተ፣ ቀርበው ለነበሩትም ለእነርሱ ሰላምን ሰበከ፤

18. ሁላችንም በእርሱ አማካይነት በአንዱ መንፈስ ወደ አብ መቅረብ እንችላለንና።

19. ከዚህ የተነሣ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጋ፣ የእግዚአብሔርም ቤተ ሰብ አባል ናችሁ እንጂ፣ ከእንግዲህ ወዲህ መጻተኞችና እንግዶች አይደላችሁም።

20. በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑ ራስ ድንጋይም ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው፤

21. በእርሱ ሕንጻ ሁሉ አንድ ላይ ተገጣጥሞ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል።

22. እናንተም ደግሞ እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚኖርበት ማደሪያ ትሆኑ ዘንድ አብራችሁ እየተገነባችሁ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤፌሶን 2