ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤፌሶን 2:14-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና፤

15. ሕግንም፣ ከትእዛዛቱና ከሥርዐቱ ጋር በሥጋው ሻረ። ዐላማውም ከሁለቱ አንድን አዲስ ሰው በራሱ ፈጥሮ ሰላምን ለማድረግ ነው።

16. ጥልን በገደለበት በመስቀሉም ሁለቱን በዚህ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ።

17. መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተ፣ ቀርበው ለነበሩትም ለእነርሱ ሰላምን ሰበከ፤

18. ሁላችንም በእርሱ አማካይነት በአንዱ መንፈስ ወደ አብ መቅረብ እንችላለንና።

19. ከዚህ የተነሣ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጋ፣ የእግዚአብሔርም ቤተ ሰብ አባል ናችሁ እንጂ፣ ከእንግዲህ ወዲህ መጻተኞችና እንግዶች አይደላችሁም።

20. በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑ ራስ ድንጋይም ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው፤

21. በእርሱ ሕንጻ ሁሉ አንድ ላይ ተገጣጥሞ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል።

22. እናንተም ደግሞ እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚኖርበት ማደሪያ ትሆኑ ዘንድ አብራችሁ እየተገነባችሁ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤፌሶን 2