ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤፌሶን 1 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉ፣ ለታመኑ፣ በኤፌሶን ለሚገኙ ቅዱሳን፤

2. ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

በክርስቶስ የሚገኝ መንፈሳዊ በረከት

3. በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤

4. በፊቱ ቅዱሳንና ነውር አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ መርጦናልና። በፍቅር፣

5. በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ፣ እንደ በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ወሰነን፤

6. ይኸውም፣ በሚወደው በእርሱ በኩል በነጻ የተሰጠን ክቡር የሆነው ጸጋው እንዲመሰገን ነው።

7. በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን፤

8. ጸጋውንም በጥበብና በማስተዋል ሁሉ አበዛልን።

9. በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ።

10. በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው።

11. ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው እንደ እርሱ ዕቅድ አስቀድሞ የተወሰንን እኛ ደግሞ በእርሱ ተመርጠናል፤

12. ይኸውም በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው።

13. እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይህም የድነታችሁን ወንጌል በሰማችሁ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተጨምራችኋል፤ አምናችሁም፣ በእርሱ በመሆን ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ታትማችኋል።

14. ለክብሩ ምስጋና ለመሆን የእግዚአብሔር የሆኑት እስኪዋጁ ድረስ፣ እርሱ ለርስታችን ዋስትና የሚሆን መያዣ ነው።

የምስጋናና የልመና ጸሎት

15. ስለዚህ በጌታ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነት፣ ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ከሰማሁበት ጊዜ አንሥቶ፣

16. በጸሎቴ እያስታወስኋችሁ ስለ እናንተ ምስጋና ማቅረብን አላቋረጥሁም።

17. የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ።

18. እንዲሁም በእርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ

19. ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኀይሉን እንድታውቁ እጸልያለሁ። ይህም ኀይል እንደ እርሱ ታላቅ ብርታት አሠራር፣

20. ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው የታየው ነው።

21. የተቀመጠውም ከግዛትና ከሥልጣን፣ ከኀይልና ከጌትነት እንዲሁም በአሁኑ ዘመን ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዘመን ቢሆን ሊሰየም ከሚቻለው ስም ሁሉ በላይ ነው።

22. እግዚአብሔርም ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛለት፤ በቤተ ክርስቲያንም፣ በማንኛውም ነገር ላይ ራስ አድርጎ ሾመው።

23. እርሷም ሁሉን ነገር በሁሉም ረገድ የሚሞላው፣ የእርሱ ሙላት የሆነች አካሉ ናት።