ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ቲቶ 3:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሰዎች ለገዦችና ለባለ ሥልጣናት እንዲገዙ፣ እንዲታዘዙና መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው።

2. እንዲሁም በማንም ላይ ክፉ እንዳይናገሩ፣ ሰላማውያን እንዲሆኑ፣ ለሰዎችም ሁሉ ከልብ የመነጨ ትሕትና እንዲያሳዩ አስገንዝባቸው።

3. ቀደም ሲል እኛ ራሳችን ማስተዋል የጐደለን፣ የማንታዘዝ፣ የተታለልን፣ ለተለያየ ምኞትና ምቾት ባሪያ ሆነን የተገዛን ነበርን፤ እየተጣላንና እርስ በርስ እየተጠላላን በክፋትና በምቀኝነት እንኖር ነበር።

4. ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣

5. ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤

6. ይህንም መንፈስ እግዚአብሔር በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤

7. ይኸውም በጸጋው ጸድቀን የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይዘን ወራሾች እንድንሆን ነው።

8. ይህም የታመነ ቃል ነው። በእግዚአብሔር ያመኑቱ መልካሙን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጡ ዘንድ እነዚህን ነገሮች አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። ይህ መልካምና ለማንኛውም ሰው የሚጠቅም ነው።

9. ነገር ግን ከንቱ ከሆነ ክርክርና ከትውልድ ሐረግ ቈጠራ፣ ከጭቅጭቅና ስለ ሕግ ከሚነሣ ጠብ ራቅ፤ ይህ ዋጋ ቢስና ከንቱ ነውና።

10. መከፋፈል የሚያመጣን ሰው አንድ ጊዜ ምከረው፤ ለሁለተኛ ጊዜ አስጠንቅቀው፤ ከዚያ ካለፈ ከእርሱ ጋር አንዳች ነገር አይኑርህ።

11. እንዲህ ዐይነቱ ሰው የሳተና ኀጢአተኛ ነው፤ ራሱንም እንደሚኰንን ዕወቅ።

12. አርጢሞንን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ እንደ ላክሁ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጵልዮን ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ክረምቱን በዚያ ላሳልፍ ወስኛለሁ።

13. ሕግ ዐዋቂውን ዜማስንና አጵሎስን በጒዟቸው ለመርዳት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ የሚያስፈልጋቸውንም ሁሉ አሟላላቸው።

14. ከእኛ ወገን ለሆኑት ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን እንዲያገኙና ኑሮአቸውም ፍሬ የሌለው እንዳይሆን ለመልካም ሥራ መትጋትን ይማሩ ዘንድ ይገባቸዋል።

15. ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ከእምነት የተነሣ ለሚወዱን ሰላምታ አቅርቡልን።ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ቲቶ 3