ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ቲቶ 1:5-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. አንተን በቀርጤስ የተውሁህ ገና ያልተስተካከለውን ነገር እንድታስተካክልና ባዘዝሁህ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው።

6. ሽማግሌ ነቀፋ የሌለበት፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ ልጆቹም አማኞችና በመዳራት ወይም ባለመታዘዝ ስማቸው የማይነሣ ይሁን።

7. ኤጲስቆጶስ የእግዚአብሔር ሥራ ባለ ዐደራ እንደ መሆኑ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባል፤ ይኸውም ትምክሕተኛ፣ ግልፍተኛ፣ ሰካራም፣ ጨቅጫቃና ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለጥቅም የሚሮጥ ሊሆን አይገባም።

8. ከዚህ ይልቅ እንግዳ ተቀባይ፣ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፣ ራሱን የሚገዛ፣ ቅን፣ ቅዱስና ጠንቃቃ ሊሆን ይገባል።

9. ሌሎችን ትክክል በሆነው ትምህርት እንዲያበረታታና ይህንኑ ትምህርት የሚቃወሙትን ይወቅስ ዘንድ እንደ ተማረው በታመነ ቃል የሚጸና መሆን አለበት።

10. ዐመፀኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉና፤ በተለይም እነዚህ ከተገረዙት ወገን ናቸው።

11. እነዚህን ዝም ማሰኘት ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ትክክል ባልሆነ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ነገር በማስተማር ቤተ ሰብን ሁሉ በመበከል ላይ ናቸውና።

12. ከራሳቸው ነቢያት አንዱ ስለ እነርሱ ሲናገር፣ “የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸታሞች፣ ክፉ አውሬዎችና ሰነፍ ሆዳሞች ናቸው” ብሎአል።

13. ይህ ምስክርነት እውነት ነው፤ ስለዚህ አጥብቀህ ገሥጻቸው፤ ይኸውም ትክክለኛ እምነት እንዲኖራቸውና

14. የአይሁድን ተረት ወይም ከእውነት የራቁትን ሰዎች ትእዛዝ እንዳያዳምጡ ነው።

15. ለንጹሓን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም ነገር የለም፤ እንዲያውም አእምሮአቸውና ኅሊናቸው የረከሰ ነው።

16. እግዚአብሔርን እናውቃለን ይላሉ፤ ዳሩ ግን በተግባራቸው ይክዱታል፤አስጸያፊዎች፣ የማይታዘዙና ለበጎ ሥራ የማይበቁ ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ቲቶ 1