ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ቈላስይስ 4:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ጌቶች ሆይ፤ እናንተም በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ስለምታውቁ አገልጋዮቻችሁን በፍትሕና በቅንነት አስተዳድሯቸው።

2. ከማመስገን ጋር ነቅታችሁ በትጋት ጸልዩ።

3. እኔ እስረኛ የሆንሁለትን የክርስቶስን ምስጢር ማወጅ እንድንችል፣ እግዚአብሔር የቃሉን በር እንዲከፍትልን ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤

4. ደግሞም መናገር እንደሚገባኝ ቃሉን በግልጽ እንድናገር ጸልዩልኝ።

5. በውጭ ካሉት ሰዎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ ተመላለሱ፤ በተገኘውም ዕድል ሁሉ ተጠቀሙ።

6. ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁል ጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን።

7. ቲኪቆስ ስላለሁበት ሁኔታ በሙሉ ይነግራችኋል፤ እርሱ የተወደደ ወንድምና ታማኝ አገልጋይ፣ በጌታም አብሮኝ ሎሌ ነው።

8. ስላለንበት ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁንም እንዲያጽናና ለዚህ ጒዳይ ወደ እናንተ እልከዋለሁ፤

9. እርሱም ከእናንተ ወገን ከሆነው ከታማኙና ከተወዳጁ ወንድማችን ከአናሲሞስ ጋር ወደ እናንተ ይመጣል፤ እነርሱም እዚህ ስላለው ሁኔታ ሁሉ ይነግሯችኋል።

10. አብሮኝ የታሰረው አርስጥሮኮስና የበርናባስ የአክስቱ ልጅ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ ስለ ማርቆስ መመሪያ ደርሶ አችኋል፤ እንግዲህ ወደ እናንተ ሲመጣ ተቀበሉት።

11. ኢዮስጦስ የተባለው ኢያሱም ሰላምታ ያቀርብላችኋል። ከተገረዙት መካከል ለእግዚአብሔር መንግሥት አብረውኝ የሚሠሩት እኔንም ያጽናኑኝ እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነርሱም አጽናንተውናል።

12. ከእናንተ ወገን የሆነው የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እርሱም ፍጹም ጠንክራችሁና ሙሉ በሙሉ ተረጋግታችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ጸንታችሁ እንድትቆሙ ዘወትር ስለ እናንተ በጸሎት እየተጋደለ ነው።

13. ደግሞም ስለ እናንተ እንዲሁም በሎዶቅያና በኢያራ ከተሞች ስላሉት ተግቶ እንደሚሠራ እኔ እመሰክርለታለሁ።

14. የተወደደው ሐኪሙ ሉቃስ እንዲሁም ዴማስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ቈላስይስ 4