ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ቈላስይስ 2:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ማንም ንግግር በማሳመር እንዳያታልላችሁ ይህን እነግራችኋለሁ።

5. ምንም በሥጋ ከእናንተ ርቄ ብገኝ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና በሥርዐት መኖራችሁንና በክርስቶስ ያላችሁን ጽኑ እምነት እያየሁ ደስ ይለኛል።

6. እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በእርሱ ኑሩ፤

7. በእርሱ ተተክላችሁና ታንጻችሁ፣ እንደ ተማራችሁት በእምነት ጸንታችሁ፣ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ።

8. በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ልማድና በዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።

9. የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በእርሱ ይኖራልና፤

10. እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል።

11. በእርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤

12. በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከእርሱ ጋር ደግሞ ተነሣችሁ።

13. እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለ መገረዝ ሙታን ሳላችሁ፣ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤

14. ሲቃወመንና ሲጻረረን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ከነሕግጋቱ በመደምሰስ፣ በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው።

15. የአለቆችንና የባለ ሥልጣናትንም ማዕረግ በመግፈፍ በመስቀሉ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ቈላስይስ 2