ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ቈላስይስ 2:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት እንዲሁም በአካል አይተውኝ ስለማያውቁ ሁሉ ምን ያህል እየተጋደልሁ እንደሆነ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤

2. ደግሞም ልባቸው እንዲጽናናና በፍቅር እንዲተሳሰሩ፣ ፍጹም የሆነውን የመረዳት ብልጥግና አግኝተው የእግዚአብሔር ምስጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ እተጋለሁ፤

3. የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በእርሱ ዘንድ ነውና።

4. ማንም ንግግር በማሳመር እንዳያታልላችሁ ይህን እነግራችኋለሁ።

5. ምንም በሥጋ ከእናንተ ርቄ ብገኝ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና በሥርዐት መኖራችሁንና በክርስቶስ ያላችሁን ጽኑ እምነት እያየሁ ደስ ይለኛል።

6. እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በእርሱ ኑሩ፤

7. በእርሱ ተተክላችሁና ታንጻችሁ፣ እንደ ተማራችሁት በእምነት ጸንታችሁ፣ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ።

8. በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ልማድና በዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።

9. የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በእርሱ ይኖራልና፤

10. እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ቈላስይስ 2