ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ቈላስይስ 1:3-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ስለ እናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ እናመሰግናለን፤

4. ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተናል፤

5. ይህም የሆነው በሰማይ ተዘጋጅቶ ከተቀመጠላችሁ ተስፋ የተነሣ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ በወንጌል የእውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ፤

6. ይህም ወደ እናንተ ደርሶአል። ይህንም ወንጌል ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ በዓለም ዙሪያ እየሠራ እንዳለ ሁሉ በእናንተም ዘንድ ፍሬ እያፈራና እያደገ ነው።

7. ይህንም ስለ እኛ የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነው፣ አብሮንም በአገልግሎት የተጠመደው ተወዳጁ ኤጳፍራ አስተማራችሁ፤

8. ደግሞም በመንፈስ ስላላችሁ ፍቅር ነገረን።

9. ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤

10. የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣

11. ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጒልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ፣

12. በቅዱሳን ርስት በብርሃን ተካፋዮች ለመሆን ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑ ነው።

13. እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤

14. በእርሱም መዋጀትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው።

15. እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤

16. ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለ ሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።

17. እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በእርሱ ነው።

18. እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር የበላይነት ይኖረው ዘንድ እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው።

19. እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ይሆን ዘንድ ወዶአልና፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ቈላስይስ 1