ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 9:10-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የርብቃ ልጆች አንድ አባት አላቸው፤ እርሱም አባታችን ይሥሐቅ ነው።

11. መንትዮቹ ገና ሳይወለዱ፣ ወይም በጎም ሆነ ክፉ ሳያደርጉ፣ የእግዚአብሔር ሐሳብ በምርጫ ይጸና ዘንድ፣

12. በሥራ ሳይሆን ከጠሪው በመሆኑ፣ “ታላቁ ታናሹን ያገለግላል” ተብሎ ተነገራት።

13. ይህም፣ “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

14. እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር አድልዎ ያደርጋልን? በፍጹም አያደርግም!

15. ለሙሴ፣“የምምረውን እምረዋለሁ፤ለምራራለትም እራራለታለሁ” ይላልና።

16. እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው።

17. መጽሐፍ ፈርዖንን፣ “ኀይሌ በአንተ እንዲታይ፣ ስሜም በምድር ሁሉ እንዲነገር ለዚህ አስነሣሁህ” ይላልና።

18. ስለዚህ እግዚአብሔር ሊምረው ለሚወደው ምሕረት ያደርግለታል፤ ልቡ እንዲደነድን የፈለገውንም ያደነ ድነዋል።

19. ከእናንተ አንዱ፣ “ታዲያ እንደዚህ ከሆነ እግዚአብሔር እስከ አሁን ለምን ይወቅሰናል? ምክንያቱም ፈቃዱን ሊቋቋም የሚችል ማን አለ?” ይለኝ ይሆናል።

20. ነገር ግን ለእግዚአብሔር መልስ የምትሰጥ አንተ ማን ነህ? “ሥራ ሠሪውን፣ ‘ለምን እንዲህ ሠራኸኝ?’ ይለዋልን?”

21. ሸክላ ሠሪ፣ ከሚሠራው ጭቃ፣ አንዳንዱን ሸክላ ለክብር፣ ሌላውን ደግሞ ለተራ አገልግሎት የማድረግ መብት የለውምን?

22. እግዚአብሔር ቊጣውን ለማሳየት፣ ኀይሉንም ለማሳወቅ ፈልጎ የቍጣው መግለጫ የሆኑትን፣ ለጥፋትም የተዘጋጁትን እጅግ ታግሦ ቢሆንሳ!

23. አስቀድሞ ለክብር ላዘጋጃቸው፣ የምሕረቱም መግለጫዎች ለሆኑት፣ የክብሩ ባለጠግነት እንዲታወቅ ይህን አድርጎ እንደሆነስ?

24. የጠራው ከአይሁድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ ወገን የሆነውን እኛን እንኳ ሳይቀር አይደለምን?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 9