ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 8:15-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. እንደ ገና የፍርሀት ባሪያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ ሳይሆን፣ “አባ፣ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋልና፤

16. የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሰክርልናል።

17. ልጆች ከሆን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።

18. የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ።

19. ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል።

20. ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተዳርጎአል፤ ይኸውም በራሱ ምርጫ ሳይሆን፣ ለተስፋ እንዲገዛ ካደረገው ከፈቃዱ የተነሣ ነው።

21. ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት እንዲደርስ ነው።

22. እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን።

23. እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ የመጀመሪያውን የመንፈስ ፍሬ ያገኘን እኛ ራሳችን የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነታችንን በናፍቆት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን።

24. በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ተስፋው የሚታይ ከሆነ ግን ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?

25. ነገር ግን ገና ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፣ በትዕግሥት እንጠብቀዋለን።

26. እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ያግዘናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፤ መንፈስ ግን በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል።

27. ልባችንንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስን ሐሳብ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለቅዱሳን ይማልዳልና።

28. እግዚአብሔር፣ ለሚወዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን።

29. እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው።

30. አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን አከበራቸው።

31. ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል?

32. ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን?

33. እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፤

34. ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 8