ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 8:11-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል።

12. ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ግዴታ አለብን፤ ይሁን እንጂ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም።

13. እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና፤ ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ፤

14. በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።

15. እንደ ገና የፍርሀት ባሪያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ ሳይሆን፣ “አባ፣ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋልና፤

16. የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሰክርልናል።

17. ልጆች ከሆን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።

18. የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ።

19. ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል።

20. ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተዳርጎአል፤ ይኸውም በራሱ ምርጫ ሳይሆን፣ ለተስፋ እንዲገዛ ካደረገው ከፈቃዱ የተነሣ ነው።

21. ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት እንዲደርስ ነው።

22. እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን።

23. እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ የመጀመሪያውን የመንፈስ ፍሬ ያገኘን እኛ ራሳችን የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነታችንን በናፍቆት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 8