ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 7:8-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ኀጢአት ግን ትእዛዙ ባስገኘው ዕድል ተጠቅሞ በእኔ ውስጥ ማንኛውንም ዐይነት አጒል ምኞት አስነሣ፤ ኀጢአት ያለ ሕግ ምዉት ነውና።

9. ሕጉ ሳይኖር ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ ከመጣ በኋላ ግን፣ ኀጢአት ሕያው ሆነ፤ እኔም ሞትሁ።

10. ለሕይወት እንዲሆን የታሰበው ያ ትእዛዝም ሞትን እንዳመጣ ተገነዘብሁ፤

11. ኀጢአት በትእዛዝ በኩል የተገኘውን ዕድል በመጠቀም አታለለኝ፤ በትእዛዝም ገደለኝ።

12. ስለዚህ ሕጉ በራሱ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፣ ጻድቅና መልካም ነው።

13. ታዲያ በጎ የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? ከቶ አይደለም፤ ነገር ግን ኀጢአት በኀጢአትነቱ ይታወቅ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር በኩል ሞትን አመጣብኝ፤ ይኸውም ኀጢአት በትእዛዝ በኩል ይብሱን ኀጢአት ይሆን ዘንድ ነው።

14. ሕጉ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለን፤ እኔ ግን ለኀጢአት እንደ ባሪያ የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ።

15. የማደርገውን አላውቅም፤ ለማድረግ የምፈልገውን አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ያን አደርጋለሁና።

16. ማድረግ የማልፈልገውን የማደርግ ከሆነ፣ ሕጉ በጎ እንደሆነ እመሰክራለሁ፤

17. እንዲህ ከሆነ፣ ይህን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው።

18. በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ፤ በጎ የሆነውን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 7