ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 5:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሶአልና።

6. ገና ደካሞች ሳለን፣ ልክ ጊዜው ሲደርስ፣ ክርስቶስ ስለ ኀጢአተኞች ሞቶአልና።

7. ለጻድቅ የሚሞት ሰው ማግኘት እጅጉን ያዳግታል፤ ለደግ ሰው ሲል ሊሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል።

8. ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል።

9. አሁን በደሙ ከጸደቅን፣ ይልቁንማ በእርሱ በኩል ከእግዚአብሔር ቊጣ እንዴት አንድንም!

10. የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከእርሱ ጋር ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም!

11. ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን።

12. ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤

13. ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም።

14. ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ።

15. ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ!

16. ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ።

17. በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ!

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 5