ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 4:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ታዲያ እንዴት ተቈጠረለት? ከተገረዘ በኋላ ነው ወይስ ከመገረዙ በፊት? የተቈጠረለት ከተገረዘ በኋላ ሳይሆን ከመገረዙ በፊት ነው።

11. ሳይገረዝ በነበረው እምነት ላገኘው ጽድቅ፣ የመገረዝን ምልክት ይኸውም የጽድቅን ማኅተም ተቀበለ፤ ስለዚህ ለሚያምኑ ነገር ግን ላልተገረዙት ጽድቅ ይቈጠርላቸው ዘንድ የሁሉ አባት ነው።

12. እርሱ ለተገረዙትም አባት ነው፤ መገረዝ ብቻ ሳይሆን፣ አባታችን አብርሃም ከመገረዙ በፊት የነበረውን የእምነቱን ፈለግ ለሚከተሉ ሁሉ ነው።

13. እርሱ የዓለም ወራሽ እንዲሆን አብርሃምና ዘሩ ተስፋን የተቀበሉት በሕግ በኩል አልነበረም፤ ነገር ግን በእምነት ከሆነው ጽድቅ ነው።

14. በሕግ የሚኖሩት ወራሾች ከሆኑ፣ እምነት የማይጠቅም፣ ተስፋም ከንቱ በሆነ ነበር፤

15. ሕግ ቊጣን ያስከትላል፤ ሕግ በሌለበት ግን መተላለፍ አይኖርም።

16. ስለዚህ ተስፋው በእምነት መጥቶአል፤ ይኸውም ተስፋው በጸጋ እንዲሆንና ለአብርሃም ዘር ሁሉ ዋስትና ይሆን ዘንድ ነው፤ ይህም በሕግ የእርሱ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን፣ በእምነት የአብርሃም ለሆኑትም ነው፤ እርሱም የሁላችን አባት ነው፤

17. ይህም “የብዙ ሕዝብ አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው፤ እርሱም ለሙታን ሕይወትን በሚሰጥ፣ ያልነበረውንም እንደ ነበረ በሚያደርግ፣ ባመነበት አምላክ ፊት አባታችን ነው።

18. “ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ ለእርሱ በተነገረው መሠረት፣ ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አምኖ የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ።

19. እርሱ የመቶ ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ፣ የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማሕፀን ምዉት እንደ ነበረ እያወቀ በእምነቱ አልደከመም።

20. ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤

21. እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር።

22. ስለዚህ፣ “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 4