ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 2:20-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. በሕጉም ካገኘኸው ዕውቀትና እውነት የተነሣ አላዋቂ ለሆኑት መካሪ፣ ለሕፃናት አስተማሪ ከሆንህ፣

21. እንግዲህ አንተ ሌሎችን የምታስተምር፣ ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ፣ ትሰርቃለህን?

22. አንተ ሰዎች ማመንዘር የለባቸውም የምትል፣ ታመነዝራለህን? አንተ ጣዖትን የምትጸየፍ፣ ቤተ መቅደስን ትመዘብራለህን?

23. አንተ በሕግ የምትመካ፣ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታዋርዳለህን?

24. ይህም “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ ዘንድ ይሰደባል” ተብሎ እንደ ተጻፈው መሆኑ ነው።

25. ሕግን የምትፈጽም ከሆነ ግዝረት ዋጋ አለው፤ ሕግን የምትተላለፍ ከሆነ ግን እንዳ ልተገረዝህ ትሆናለህ።

26. ያልተገረዙት ሕጉ የሚያዝዘውን የሚፈጽሙ ከሆነ፣ እንደ ተገረዙ አይቈጠሩምን?

27. አንተ የተጻፈ ሕግ፣ ግዝረትም ቢኖርህ፣ ሕግ ተላላፊ በመሆንህ፣ በሥጋ ያልተገረዘው ለሕግ በመታዘዙ ይፈርድብሃል።

28. አንድ ሰው ለይምሰል በውጫዊው ብቻ ይሁዲ ልሁን ቢል ይሁዲ አይሆንም፤ እውነትኛ ግዝረትም ውጫዊና ሥጋዊ ሥርዐት አይደለም።

29. ዳሩ ግን አንድ ሰው ይሁዲ የሚሆነው በውስጣዊ ማንነቱ ይሁዲ ሆኖ ሲገኝ ነው። ግዝረትም ግዝረት የሚሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ በመንፈስ የልብ ግዝረት ሲኖር ነው። እንዲህ ያለው ሰው ምስጋናው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 2