ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 2:14-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸውም እነርሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸው።

15. ኅሊናቸው ስለሚመሰክር፣ ሐሳባቸው ስለሚከሳቸው፣ ደግሞም ስለሚከላከልላቸው የሕግ ትእዛዝ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያሉ።

16. ይህም በወንጌል እንደማስተምረው እግዚአብሔር በሰው ልብ የተሰወረውን በክርስቶስ በኩል በሚፈርድበት ዕለት ግልጽ ይሆናል።

17. አንተ ይሁዲ ነኝ ካልህ፣ በሕግ የምትተማመንና ከእግዚአብሔር ጋር ባለህ ግንኙነት የምትኵራራ፣

18. በሕግ በመመራትህም ፈቃዱን ዐውቀህ ፍጹም የሆነውን ለይተህ ከያዝህ፣

19. ለዕውሮች መሪ፣ በጨለማ ላሉትም ብርሃን መሆንህን ርግጠኛ ከሆንህ፣

20. በሕጉም ካገኘኸው ዕውቀትና እውነት የተነሣ አላዋቂ ለሆኑት መካሪ፣ ለሕፃናት አስተማሪ ከሆንህ፣

21. እንግዲህ አንተ ሌሎችን የምታስተምር፣ ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ፣ ትሰርቃለህን?

22. አንተ ሰዎች ማመንዘር የለባቸውም የምትል፣ ታመነዝራለህን? አንተ ጣዖትን የምትጸየፍ፣ ቤተ መቅደስን ትመዘብራለህን?

23. አንተ በሕግ የምትመካ፣ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታዋርዳለህን?

24. ይህም “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ ዘንድ ይሰደባል” ተብሎ እንደ ተጻፈው መሆኑ ነው።

25. ሕግን የምትፈጽም ከሆነ ግዝረት ዋጋ አለው፤ ሕግን የምትተላለፍ ከሆነ ግን እንዳ ልተገረዝህ ትሆናለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 2