ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 12:6-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. እንደ ተሰጠን ጸጋ የተለያዩ ስጦታዎች አሉን፤ ለአንዱ የተሰጠው ስጦታ ትንቢት መናገር ከሆነ፣ እንደ እምነቱ መጠን ይናገር።

7. ማገልገል ቢሆን ያገልግል፤ ማስተማርም ከሆነ ያስተምር፤

8. መምከር ከሆነ ይምከር፤ ለሌላቸው መለገስ ከሆነም አብዝቶ ይለግስ፤ ማስተዳደር ከሆነም በትጋት ያስተዳድር፤ ምሕረት ማድረግ ከሆነም በደስታ ይማር።

9. ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ክፉ የሆነውን ሁሉ ተጸየፉ፤ በጎ ከሆነው ነገር ጋር ተቈራኙ።

10. እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ።

11. ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ።

12. በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ።

13. ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ፤ እንግዶችን ተቀበሉ።

14. የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ።

15. ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያዝኑም ጋር እዘኑ።

16. እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ።

17. ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ።

18. ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።

19. ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቊጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።

20. ይልቁንስ፣“ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ቢጠማም አጠጣው።ይህን በማድረግህም የእሳት ፍም በራሱ ላይ ትከምራለህ።”

21. ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 12