ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 10:11-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።”

12. በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤

13. “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”

14. ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ?

15. ካልተላኩስ እንዴት መስበክ ይችላሉ? ይህም፣ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

16. ነገር ግን የሰሙት ሁሉ የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም፤ ኢሳይያስም፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኖአል?” ብሎአልና።

17. እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው።

18. ነገር ግን አልሰሙ ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በርግጥ ሰምተዋል፤“ድምፃቸው በምድር ሁሉ፣ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ተሰማ።”

19. ደግሜም እጠይቃለሁ፤ እስራኤል አላስተዋሉ ይሆን? በቅድሚያ ሙሴ እንዲህ ይላል፤“ሕዝብ ባልሆኑት አስቀናቸዋለሁ፤ማስተዋል በሌለው ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ”

20. ኢሳይያስም በድፍረት፣“ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፤ላልጠየቁኝ ራሴን ገለጥሁላቸው” ይላል።

21. ስለ እስራኤል ግን፣“ወደማይታዘዝና እሺ ወደማይል ሕዝብ፣ቀኑን ሙሉ እጄን ዘረጋሁ” ይላል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 10