ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

መቶ አርባ አራት ሺሁ መታተማቸው

1. ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማእዘኖች ቆመው አየሁ፤ እነርሱም ነፋስ በምድር ወይም በባሕር፣ ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሶች ያዙ።

2. ከዚያም የሕያው አምላክ ማኅተም ያለው ሌላ መልአክ ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ እርሱም ምድርንና ባሕርን ለመጒዳት ሥልጣን የተሰጣቸውን አራቱን መላእክት በታላቅ ድምፅ እንዲህ አላቸው፤

3. “በአምላካችን አገልጋዮች ግንባር ላይ ማኅተም እስከምናደርግባቸው ድረስ ምድርን ወይም ባሕርን፣ ወይም ዛፎችን አትጒዱ።”

4. የታተሙትንም ቊጥር ሰማሁ፤ እነርሱም ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ፤

5. ከይሁዳ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣

6. ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣

7. ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣

8. ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፣ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።

ነጭ ልብስ የለበሱ እጅግ ብዙ ሕዝብ

9. ከዚህም በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው፣ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው ነበር።

10. በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ጮኹ፤“ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው፣የአምላካችንና የበጉ ነው።”

11. መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ፣ በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤

12. እንዲህም ይሉ ነበር፤“አሜን፤ውዳሴና ክብር፣ጥበብ፣ ምስጋናና፣ ሞገስ፣ኀይልና ብርታትም፣ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤አሜን።”

13. ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” አለኝ።

14. እኔም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ታውቃለህ” አልሁት።እርሱም እንዲህ አለኝ፤ እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው “አንጽተዋል።

15. ስለዚህ፣“በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሆነው፣ቀንና ሌሊት በመቅደሱ ያገለግሉታል፤በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑንበላያቸው ይዘረጋል፤

16. ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ከዚህም በኋላ አይጠሙም፤ፀሓይ አይመታቸውም፤ሐሩሩም ሁሉ አያቃጥላቸውም፤

17. ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለውበግ እረኛቸው ይሆናል፤ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”