ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 3:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. በትዕግሥት እንድትጸና የሰጠሁህን ትእዛዜን ስለ ጠበቅህ፣ እኔ ደግሞ በምድር ላይ የሚኖሩትን ሊፈትናቸው በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ።

11. ቶሎ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጥብቀህ ያዝ።

12. ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ውስጥ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም። የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ይኸውም ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ አዲሱን ስሜንም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።

13. መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።

14. “በሎዶቅያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ አሜን የሆነው፣ ደግሞም ታማኝና እውነተኛ ምስክር የሆነው፣ የእግዚአብሔርም ፍጥረት ገዥ የሆነው እንዲህ ይላል፤

15. ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ እንዳልሆንህ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ ብትሆን በወደድሁ ነበር።

16. እንግዲህ ለብ ያልህ ብቻ እንጂ ትኵስ ወይም ቀዝቃዛ ስላልሆንህ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው።

17. ‘ሀብታም ነኝ፤ ባለጠጋ ነኝ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና፣ የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም።

18. ስለዚህ ሀብታም እንድትሆን፣ በእሳት የነጠረ ወርቅ እንድትገዛ፣ የዕራቍትነትህ ኀፍረት እንዳይታይ፣ ነጭ ልብስ እንድትለብስና ለማየት እንድትችል ዐይንህን በኵል እንድትኳል እመክርሃለሁ።

19. እኔ የምወዳቸውን እገሥጻለሁ፤ እቀጣለሁም። ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ።

20. እነሆ፤ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።

21. እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በእርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።

22. መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 3